ሰው ይናፍቀኛል
አገሩን የሚወድ በእውነተኛ ፍቅር
ነገን የሚመለከት በትናንት የማይኖር
ሰውን በሰውነት ዘወትር የሚያከብር
ሰው ይናፍቀኛል ለሰው ልጅ የሚኖር
ክፋት ምቀኝነት ተንኮል የሌለበት
ልቡ በጥላቻ ያልተሸነፈበት
በዘመን መካከል የማይለዋወጥ
የኋላውን ረስቶ ወደ ፊት የሚሮጥ
ሁሌ ሰው ያምረኛል ፍቅር የሚሰጠኝ
በደካማ ጎኔ ቆሞ የሚረዳኝ
ሳጠፋ የሚመክረኝ በቅንነት መንፈስ
ድካሜን የሚሸከም ብርታቴን የሚያወድስ
ሰው ይናፍቀኛል ሰውን የሚያፈቅር
ወደ ፊት እያየ በትናንት የማይኖር
በትዕግስት እንድሮጥ አቅም የሚሆነኝ
ችግሬን ተጋርቶ ደስታ የሚሰጠኝ
ህልሜን የሚፈታ ምኞቴን የሚካፈል
ጉልበቴ ሲደክም ሸክሜን የሚያቃልል
በፍቅር እየኖረ ፍቅር የሚያስተምረኝ
ሰው ይናፍቀኛል ሁሌ የሚኖር አብሮኝ
አማራ ነህ ትግሬ ወይስ ነህ ኦሮሞ
እያለ የማይጮህ ከምባታና ጋሞ
ነፍሴን የማያዝል በነገር ቡትቶ
ሰው ይናፍቀኛል ሰው የሚሆን ሰርቶ
በጥላቻ የማይኖር ፍቅር የበዛለት
ለአገር ለወገኑ የሚኖር በቅንነት
በአዲስ አስተሳሰብ ነፍሱ የተሞላ
በዘረኝነት መርዝ ጉልበቱ ያልላላ
ሁሌ የሚመለከት በፍቅር መነፅር
ያለውን አካፍሎ ለወገኑ የሚኖር
ሰው ይናፍቀኛል ነገን የሚያሳየኝ
በኢትዮጵያዊነት ልቤን የሚገዛኝ።
ጥር 19 ቀን 2006 ዓ•ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በቅርብ እውን ይሆናል!!!
No comments:
Post a Comment