Wednesday, October 2, 2013

ስለህወሓት ፀረ-ኢትዮጵያ አካሄድ የተሸፈኑ ምስጢሮች (ገብረመድህን አርኣያ)

ስለህወሓት ፀረ-ኢትዮጵያ አካሄድ የተሸፈኑ ምስጢሮች (ገብረመድህን አርኣያ)

የህወሓትን ፀረ-ኢትዮጵያ አካሄድና ዓላማ በመቃወም የሕይወት ማስዋዕትነት የከፈሉ አመራር ነበሩ ወይ? ከነበሩስ እነማን ናቸው?
ገብረመድህን አርኣያ ከአስውትራሊያ
ገሰሰው አየለ፣ አግአዚ ገሰሰ፣ ሙሴ መሃሪ ተክሌ፣ አጽብሃ ዳኛው እና ዶ/ር አታክልት ቀጸላ Gessesew Ayele, Agazi Gessese, Musse Mahri Tekle, Atsbeha Dagnachew and Dr. Atakilt Ketswela
ከዚህ ቀጥለን የምንመለከተው ትኩረት ያልተሰጠውን ተሸፍኖ የነበረውን እና የህወሓት መሪዎች፣ በሕይወት ያሉትም የሞቱትም፣ ከወያኔ የተባረሩ አመራርም ጉዳዩ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ተዳፍኖ እንዲቀር ከባድ ጥረት እያደረጉበት ያለውን ነው።
በህወሓት የተፈጸመው እውንተኛ ታሪክና አሰቃቂ ወንጀሎች፣ የህወሓት አመራር በኢትዮጵያ ሀገራችን አሁንም እየፈፀሙት የሚገኘው ግፍ በግልጽ ተጽፎ የወያኔ ጥቁር ታሪክ ለሕዝብ የሚቀርብበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። አሁንም እየቀረበ ነው።
ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ለትግል የተሰማራው በየካቲት 11 ቀን 1967 ደደቢት በረሃ እንደመሸገ ማሀብር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገብት) የተዘጋጀው ፕሮግራም የተረከበው ተሓህት ወይም የዛሬው ስሙ ሀወሓት ነው።
ተሓህት ትግሉን በጀመረበት ወቅት ጥቂት ከነበሩት ታጋዮች ሊመሩን ይችላሉ ብሎ ከመረጣቸው መካከል፤ 1. አረጋዊ በርሄ፣ ሊቀመንበር 2. ዘርኡ ገሰሰ 3. ግደይ ዘርአጽዮን 4. ገሰሰው አየለ 5. አባይ ፀሃየ 6. ሥዩም መስፍን 7. አለምሰገድ መንገሻ 8. አስፍሃ ሃጎስ ተመርጠው ተሓህትን መርተዋል።
በዚህ ጊዜ ነበር የማገብትን ውርስ ተሓህት ተረከበው ብሎ በጊዜው የነበረ ታጋይ ደስታውን የገለጸው። ውርስ ማለት ፕሮግራሙ ነው። በጊዜው የነበረ ሁሉም ታጋይ ግን የፕሮግራሙን ይዘትና ምንነትቱን አያውቅም ነበር። ይህ ፕሮግራም ነበር በ1968 ቀስ በቀስም ተሓህትን ለሁለት የመሰንጠቅ አደጋ የፈጠረበት። … (ሙሉውን ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!)

የአፈፃፀም ችግር ያለው ጥሩ ፖሊሲ የለም!

የአፈፃፀም ችግር ያለው ጥሩ ፖሊሲ የለም!

የአንድ ፖሊሲ ስህተትነት እንዴት ይታወቃል?
Abraha Desta
አንደኛ ከጅምሩ የሐሳብ consistency ሲያጣ፣ ምክንያታዊነት መሰረት ያደረገ ወደ ልማታዊ ግብ የሚያደርስ የሐሳብ ትስስር ከሌለው።
ሁለተኛ የምክንያታዊነት ጉድለቱ በግልፅ የሚታይ ሲተገበር ነው። የወጣውን ፖሊሲ ሊተገበር ካልቻለ፣ ማለት የአፈፃፀም ችግር ካጋጠመው ፖሊሲው ችግር እንዳለው ወይ ስህተት እንደሆነ ማሳያ ነው። ፖሊሲ አፈፃፀም ነው። ፖሊሲ የሚወጣው ሊፈፀም ነው። የአፈፃፀም ችግር የፖሊሲው ችግር ነው።
‘ጥሩ ፖሊሲ ተቀርፆ በፖሊሲው ፈፃሚዎች ብቃት ወይ ተነሳሽነት ማነስ ሳይተገብር ወይ ሳይፈፀም ቢቀርስ?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን ፖሊሲ ሲወጣ ዓላማውና የአፈፃፀም ሂደቱ በደንብ መቀመጥ አለበት። በአፈፃፀም ሂደት … እንዴት እንደሚፈፀም፣ መቼ እንደሚፈፀም፣ ማን እንደሚፈፅመው፣ የፈፃሚዎቹ የማስፈፀም ዓቅም ምን ድረስ እንደሆነ … ግምት ዉስጥ ይገባል።
ባጭሩ የፖሊሲ ዋነኛ ተግባር አፈፃፀም እስከሆነ ድረስ የፈፃሚዎች የመተግበር ዓቅም ግምት ዉስጥ ያስገባል። ይህንን ግምት ዉስጥ ካላስገባ ፖሊሲው ችግር አለበት። ስለዚህ የአፈፃፀም ችግር ያለበት ጥሩ ፖሊሲ ሊኖር አይችልም።
ፖሊሲ ከሕገመንግስት ይለያል። ሕገመንግስት የመንግስትና የዜጎች የስምምነት ሰነድ ነው። በስምምነቱ የተካተቱ ነጥቦች ለሁለቱም ወገኖች ጥሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም ስምምነት ነው። ግን የስምምነት ነጥቦች ጥሩ ሁነው ሳለ በአንዱ ወገን ወይ በሁለቱም ወገኖች ሊጣሱ ይችላሉ። ሕገ መንግስቱ (ስምምነቱ) ስለተጣሰ ግን እንደፖሊሲው ስህተት ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሕገመንግስት የሚወጣው ሊከበር ሲሆን ፖሊሲ ግን ሊፈፀም ነው።
ሕገመንግስት አለመጣስ፣ ማክበር ነው። አለመጣስ አለማድረግ ነው። ስለዚህ ተነሳሽነቱና ቅንነቱ ካለ ሕገ መንግስት ለማክበር የምናሳርፈው ጥረት የለም። ሕገመንግስት ለመጠበቅ ጥረት የሚያስፈልግ ሕግ የሚጥሱ አካላት ሲኖሩ ብቻ ነው። በሕገመንግስት ተግባር የሚያስፈልግ ያለውን ለመጠበቅ ነው። በፖሊሲ ግን ለትግበራው ሲባል ከጅምሩ የምናሳርፈው ጥረት አለ። ፖሊሲና ተግባር አብረው የሚሄዱ ናቸው።
ግን ሁሉም ሕገመንግስት (ወይ ስምምነት) ትክክል ነው ማለት አይደለም። ችግር ካለው ሊሻሻል ይገባል። የማይፈፀም ፖሊሲም እንደገና መፈተሽ አለበት።
It is so!!!

ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀው ፖለቲካ

ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀው ፖለቲካ

ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀው ፖለቲካ
‹‹የምን ይቅርታ? ለሕዝብና ለአገር ዕድገት ነው የተነሳነው፡፡ በትግሉ ሒደት ስህተት ፈጽመናል፤ ስህተቱ የትግሉ አካል ነው፡፡ ዘውዳዊ ሥርዓቱን ጥለናል፤ የኢትዮጵያንም ሕዝብ ነፃ አውጥተናል፡፡
የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ይናገሩ፡፡ ከወላይታ የመጣውና ከአናሳ ሃይማኖት የመጣው ግለሰብ አገር የሚመራው በእኛ ትግል ምክንያት ነው፡፡ በማያውቀውና ባላነበበው ታሪክ የበሰበሰ ይለናል? የመጀመሪያ ዘመቻችን የዕውቀት ዘመቻ መሆን አለበት፡፡››
ይህን የተናገሩት የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ሲሆኑ መልስ እየሰጡ የነበረው ደግሞ ፓርቲያቸው ኢሕአፓንና የትግል አጋሮቻቸውን አስመልክቶ ትችት ላቀረበ አንድ ወጣት ነበር፡፡ ወጣቱ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ዘግናኝና ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡ መድረክ ላይ ያላችሁት ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በተለያየ መስመር ተሰማርታችሁ ባመናችሁበት አቋም የአገሪቱን የፖለቲካ እመርታ ለማስለወጥም ሆነ ለማሳደግ የራሳችሁን ሚና ተጫውታችኋል፡፡ የ60ዎቹና 70ዎቹ ትንታግ ትውልድ ዳፋ አሁንም ባለንበት የፖለቲካ ተግባራዊ ሁኔታ ላይ በእጅጉ ሲንፀባረቅ ነው የምናየው፡፡ መጠላላቱና ጥቅመኝነቱ እንዳለ ነው፡፡ እዚህ አዳራሽ ውስጥ በመኢሶን፣ በኢሕአፓና በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ የታገላችሁ ሰዎች አላችሁ፡፡ ያ የከሰረ፣ የበሰበሰ፣ የተቀበረና የሞተ የትግል ውጤት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ግን አሁንም ሰንኮፉ አልለቀቀንም፡፡ በምትጽፏቸው መጽሐፎችና በምታቀርቧቸው ፕሮግራሞች ላይ አሁንም የቀይ ሽብር ትውስታዎች እንዳሉ እናያለን፡፡ መቼ ነው ኢሕአፓዎችና መኢሶኖች በአደባባይ ወጥታችሁ የሠራነው ስህተት፣ የፈጸምነው በደል ይኼ ነበር፤ ትውልድ ከእኛ ተምሮ እዚህ ላይ ትኩረት ያድርግ በማለት ይቅርታ የምትጠይቁት? አሁንም እየተታኮሳችሁ ነው፣ ዛሬም ኢትዮጵያን የምትተረጉሙት በተለያየ መንገድ ነው፤›› በማለት ነበር አስተያየት የሰጠው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ መሆኑን የገለጸው ወጣት አስተያየት ቁጣን የቀሰቀሰው በፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ መድረኩ ላይ የጥናት ሥራዎቻቸውን ያቀረቡትን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ጨምሮ ከታዳሚዎቹ ውስጥ “Tower in the Sky” በተሰኘ መጽሐፏ በአጭር ጊዜ ዝነኛ የሆነችው የኢሕአፓ የቀድሞ ታጋይ ሕይወት ተፈራና ከኢሕአፓ መሥራቾች አንዱ የሆነው የብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልን ጨምሮ፣ የ1960ዎቹ እና የ1970ዎቹ ትግል አካል የነበሩ በርካታ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡
መስከረም 19 ቀን በደሳለኝ ሆቴል የተዘጋጀው ሕዝባዊ መድረክ በአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት መታሰቢያ፣ በኢንተር አፍሪካ ግሩፕና በጀስቲስ አፍሪካ ትብብር ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማው ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይከሰት ምን ማድረግ ይገባል? በሚለው ጥያቄ ላይ ውይይት ለማድረግ ቢሆንም፣ በመድረኩ ላይ የተንፀባረቁት የሐሳብ ልዩነቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬም ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀ መሆኑን ያረጋገጠ ነበር፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን ጨምሮ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የፖለቲካ ትግል ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት የዛሬዋ ኢትዮጵያን የመንግሥትና የተቃውሞ ፖለቲካ መዋቅርን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ወሳኝ ዘርፎችን በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዕድሜና በጤና ምክንያት ከመድረኩ ሲገለሉም ከማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም የተቀዳውን አካሄዳቸውን ለአዲሱ ትውልድ እያወረሱ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም ዲሞክራሲን የሚሰብከውን ሕገ መንግሥት፣ ከሕገ መንግሥት ጀርባ ያለው ሌላው ሕገ መንግሥት በሚባለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዲሸረሸር ያደረገው ከዚሁ ከማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር ካለው ጥብቅ ቁርኝት አንፃር እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ የቡድኖቹ ቅርበትና ልዩነት ርዕዮተ ዓለምን መሠረት ያደረገና ከኋላ ታሪክ መቀዳቱ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ለውጥ እጅግ አዝጋሚ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በመድረኩም የተስተዋለው ይኼው እውነታ ነው፡፡ የወጣቱ ትውልድ አባላት ጥያቄ በአላዋቂነት ነው የተዘጋው፡፡ አንድ የመኢሶን አባል የነበሩ ግለሰብ ጥያቄም በተቃውሞ ነው የተመለሰው፡፡ ለነገሩ ግለሰቡም ውስብስቡን ፖለቲካ እጅግ አቃለው ኢሕአፓ ለኤርትራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ማሰቡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለውጭ ኃይል አሳልፎ ከመስጠት ጋር ነው ያያያዙት፡፡ ኤርትራ በወቅቱ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡ የኢሕአፓ አባል የነበሩ ምሁራን የፓርቲውን ስህተት ይደፋፍናሉ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ አልነበረም፡፡ ለዘመኑ ወጣት አክብሮት አትሰጡም ተብለውም ሲተቹ አንድ ዕድሜያቸው ገፋ ያለ ግለሰብ፣ ‹‹የዘመኑ ወጣት እንደያኔው በቀላሉ አይነዳም›› ሲሉ፣ የአብዮቱ ተሳታፊዎች በጥቂት ወራት ባዕድ የሆነ የሌላ አገር ርዕዮተ ዓለምን ወደ ኢትዮጵያ አውድ ለመቀየር እንኳን ሳይሞክሩና በጥልቀት ሳይረዱት በመከተላቸው አገሪቱ መታመሷን ሲገልጹም ድጋፍ አላገኙም፡፡
ወጣቱ ትውልድ ከእናንተ ምን ይማር? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ከመድረክ ጥናት አቅራቢዎቹና ከታዳሚዎቹ መካከል የተለያዩ ምላሾች ቀርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የዕውቀትን አስፈላጊነት መማር ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን ሁኔታ በማርክስ ጽሑፎች መመለስ አይቻልም ነበር፡፡ መቻቻልና መደማመጥ መማር ይቻላል፡፡ ስህተትን መቀበል መማር ይቻላል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ በብቸኝነት ልንይዝ እንደማይገባ ልንማር ይገባናል፡፡ ታሪካችን ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ እያነፃፀርን ልንረዳው ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡
በአብዮቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የዳያስፖራው ሚና ምን ነበር? የመኢሶንና የኢሕአፓ ልዩነት ምን ያህል ሰፊ ነበር? መኢሶን ወይም ኢሕአፓ ከሕዋሓት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ከመኢሶን ወይም ከኢሕአፓ አንዳቸው በደርግ ቦታ ሥልጣን ቢይዙ ቀይ ሽብር እንደማይኖር ምን ማረጋገጫ አለ? በአሁኑ ወቅት የአደባባይ ምሁራን የጠፉት ከቀይ ሽብር ጋር በተያያዘ ነው ወይ? ቀይ ሽብር ለመንግሥትና ለሕዝብ አሉታዊ ግንኙነት እንዴት ነው አስተዋጽኦ ያደረገው? በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዴት መፍጠር ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎችም ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩ ሲሆን የተወሰኑት ብቻ ምላሽ አግኝተዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ መኢሶንና ኢሕአፓ ‹እናሸንፋለን› እና ‹እናቸንፋለን› ከሚለው እጅግ የዘለለ ልዩነት እንደነበራቸው በመጥቀስ ልዩነታቸው ጥቃቅን እንዳልነበር ያመለከቱ ሲሆን፣ ሁለቱም ድርጅቶች በትክክል ማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ነበሩ ለማለት እንደማይቻልም አስረድተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ልዩነቱ የፖለቲካ ሥልጣን ጉዳይ እንደነበር አስገንዝበው፣ ደርግም ሆነ እሱን ለመፋለም የተሠለፉት ኃይሎች ጥፋተኞች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ መኢሶንና ኢሕአፓ በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ እስከ ጥር ወር 1967 ዓ.ም. ድረስ አንድ የነበሩ ቢሆንም፣ መኢሶን ‹ሒሳዊ ድጋፍ› በሚል ከደርግ ጋር ለመሥራት መወሰኑ በሥልጣን አያያዝ አካሄድ ላይ መሠረታዊ ልዩነት እንዲኖራቸው ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
የመኢሶንና የኢሕአፓን የአደባባይ ይቅርታ በተመለከተ ዶ/ር ካሳሁን በግለሰቦችና በመጻሕፍት ውስጥ ይቅርታቸው ቢታይም፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቶቹ ሕልውና ስለሌላቸው ያን ማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ በስሜት መናገር እንደማይጠቅም የገለጹት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ድርጅቶቹ ይቅርታ የመጠየቅ ፍላጎት የሌላቸው መነሻቸው ለኢትዮጵያ በጎ ነገር ለመሥራት መሆኑን በመጥቀስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ የያኔውን የዳያስፖራ ተፅዕኖ በተመለከተ አስተያየት ሲሰጡ የያኔው የዲያስፖራ ተፅዕኖ እንዳሁኑ ጠንካራ እንዳልነበር አስገንዝበዋል፡፡
አንድ አስተያየት ሰጪ የቀይ ሽብር ተጎጂዎችን ለመደገፍና በእነሱ ዙሪያ የተሟላ መረጃ የመስጠት ችግር እንዳለም ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል በቀይ ሽብር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር በውል ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ቀይ ሽብር እንዳይደገም
የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሲመረቅ የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት መታሰቢያ ስብሰባ አዳራሹ ላይ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ የመታሰቢያው ጊዜያዊ የአመራር ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ እ.ኤ.አ. ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. መሠረት ድንጋይ ሲጣል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቦታውን ልዩ አብነት አስመልክቶ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር በጥሞና ማውሳታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ቦታው የቀድሞው የከርቸሌ እሥር ቤት እንደነበርና ‹ዓለም በቃኝ› የተሰኘ በጣልያን ወረራ ጊዜና በኋላም በደርግ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሰቃዩበትና የገደሉበት ቦታ እንደነበርም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡
መታሰቢያው ቀይ ሽብርን ጨምሮ በሩዋንዳና በደቡብ አፍሪካ የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋትና የአፓርታይድ ጭቆና፣ ባርነትና ቅኝ ግዛት የሚታወሱበት እንደሚሆንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በመታሰቢያው ብዙኃን ጉዳተኞችን ከማስታወስ አልፎ በአፍሪካውያን መሠረታዊ ለውጦች ላይ መሰል አደጋ መቼም በማንም ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች አቋም የሚያንፀባርቁበት ነው፤›› በማለትም ዋነኛ ዓላማውን አመልክተዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር ስብሰባ በሩዋንዳ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 10 እስከ 12 ቀን 2012 መካሄዱን የጠቆሙት ፕሮፌሰር አንድሪያስ፣ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን ለማስታወስ በየዓመቱ የ100 ቀን የሐዘን ጊዜ መኖሩን አስታውሰው፣ በኢትዮጵያም ለቀይ ሽብር ሰማዕታት የሐዘን ጊዜ መመደብ ያስፈልግ ይሆን ወይ? ብለው እንዲጠይቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተደረገው የመታሰቢያው ስብሰባ ስለ ቀይ ሽብር የሚመለከታቸው አካላት ሐሳብ በመለዋወጥ የተሻለ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቀይ ሽብር ፖለቲካዊ አንድምታዎች
የ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት ሒደት የተጀመረውና አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹን እያሳደረ የተጓዘው የዳበረ ሰላማዊ ፖለቲካ ሽግግር ባሕልም ሆነ የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ባልተለመደበትና ባልዳበረበት አጠቃላይ ማዕቀፍ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ አብዮቱ ተስፋ እንደተደረገው ሰላማዊና ከደም መፋሰስ የፀዳ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡
ለቀይ ሽብር መከሰት ዋነኛው ምክንያት በለውጡ እንቅስቃሴ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ በቂ የሐሳብ ልውውጥ ተደርጎ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የአብዮቱ መቀጣጠል ድንገተኛነትና ግብታዊነት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ፍላጎቶችን አቀናጅቶ ሒደቱን መምራት የሚችል ግንባር ቀደም ድርጅት ተዘጋጅቶ አለመቆየቱ እንደሆነ ዶ/ር ካሳሁን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተባለው ድርጅት በርካታ አባላትና ደጋፊዎችን አፍርቶ የጀመረው የከተማ ሽምቅ ውጊያ የበርካታ ሺሕ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውንና በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ሕይወት ያናጋውን ቀይ ሽብር ተብሎ የሚታወቅ ክስተት ማስከተሉን የጠቆሙት ዶ/ር ካሳሁን፣ ይህ አሉታዊ ውጤት በአገሪቱና በዜጎቿ ላይ ያደረሰውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ተቋቁሞ በትክክለኛ መስመር ላይ የተመረኮዘ ግንባታና ተሃድሶ ለማካሄድ እስካሁንም ድረስ እጅግ ሰፊ ልፋትና ጥረት የሚጠይቅ ዓብይ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ በቀይ ሽብር የተነሳ ሦስት መሠረታዊ የፖለቲካ አንድምታዎች መድረሳቸውን ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ተፅዕኖ ከመንግሥትና ከሕዝብ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ በአብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል ባሕልና እምነት መንግሥት ሕዝብን ከአደጋና ክፉ ነገሮች የሚጠብቅ፣ የሚከላከልና የሚታደግ አካል ተደርጐ ሲወሰድ የነበረበት ሁኔታ ቀይ ሽብር ባደረሳቸው ጥፋቶችና መናጋቶች የተነሳ ተቀይሮ የሕዝብ አስተዳዳሪ የሆነው መንግሥት በአጥፊነት፣ በግፈኝነትና በመከራ ምንጭነት በሚታይበት ሁኔታ የመተካት ዝንባሌ በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ግንኙነት የጥርጣሬ፣ የፍርኃትና ያለመተማመን ገጽታዎች እንዲላበስ አስገድዷል፤›› ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ተፅዕኖ ከዜጎች የፍርኃት ስሜት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ዶ/ር ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ “ቀይ ሽብር በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያሳደረው የፍርኃትና የጭንቀት ድባብ በርካታ ዜጎች በአገሪቱ የፖለቲካ ዋና ዋና ጉዳዮች በንቃት የመሳተፍና የየበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ የማድረግ አስፈላጊነትን በርቀት እንዲሸሹና በገለልተኛነት እንዲያዩት የሚያደርግ አዝማሚያ አስፍኗል፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
ሦስተኛው ተፅዕኖ ከዜጎች ባሕሪ መለወጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ዶ/ር ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡ “በቀይ ሽብር ሳቢያ ብዙዎች የፖለቲካ አስመሳይነት፣ የአድርባይነትና የለዘብተኝነት ባህሪያትን ተላብሰው ነገሮችን ከአጭር ጊዜና ግላዊ ጥቅምና ፍላጎት ማሟያ አንፃር ብቻ የመመልከት አጉል ባሕሪ እንደ ዓላማ እንዲይዙ አድርጓል፡፡”
ዶ/ር ካሳሁን ስለ ቀይ ሽብር በተደጋጋሚ ከማውሳትና የድርጊቱን ተዋናዮች ከማውገዝና ከመኮነን በዘለለ፣ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይደገሙ በተለያዩ ጎራዎች ተሰልፈው ደም የተቃቡና ቂም የተያያዙ ወገኖችን በማገናኘት ከቁርሾ ከመራራቅ ተቆጥበው የየግላቸውና የጋራ ስህተቶቻቸውን የሚገመግሙባቸውን መድረኮች በማመቻቸት፣ ለጋራ ጥቅምና አብሮነት በትብብር የሚሠሩበትን ሁኔታ ማገዝና ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የተፈጸመውን ሳይረሱ ይቅር መባባል እንዳለባቸውም ዶ/ር ካሳሁን መክረዋል፡፡
የቀይ ሽብር ታሪካዊ ዳራዎች
ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ለቀይ ሽብር የዳረገው አብዮት በ1966 ዓ.ም. ሲከሰት አገሪቱ ለአብዮት ፈጽሞ ዝግጁ እንዳልነበረች አስረድተዋል፡፡ በዓለም ታሪክ እጅግ ጥቂት የሆኑት ማኅበራዊ አብዮቶች የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ሥርዓትና ማኅበራዊ መዋቅር ሙሉ በሙሉ የሚቀይሩ፣ ኅብረተሰቡን የሚመራውን ገዥ ርዕዮተ ዓለም ቀይረው በሌላ የሚተኩና በኅብረተሰቡ በኩል ትልቅ ምስቅልቅል የሚያመጡ ክስተቶች በመሆናቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ጥቂት ማኅበራዊ አብዮቶች መካከል አንዱን በ1966 ዓ.ም. ማስተናገዷንም ገልጸዋል፡፡
ከ1933 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ባለው ጊዜ አገሪቱ በግንባታና በለውጥ ላይ የነበረች ብትሆንም፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የራሱ ለውጥ የፈጠራቸውን የለውጥ ኃይሎች ሊቆጣጠራቸውና ሊቀድማቸው እንዳልቻለ ፕሮፌሰር ሽፈራው አስታውሰዋል፡፡ ከአራት እስከ አምስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በ1950ዎቹ ሲመዘገብ በዓለም ባንክ ጭምር የተከበረ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር ሽፈራው፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የሕዝብ ብዛት እንዲጨምር ገዳይ በሽታዎችን በመቆጣጠር አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ የሕዝቡ ብዛት ግን ቤት አልበኝነትንና ፍፁም ድህነትን በማምጣት የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄ እንዲያነሳ መጋበዙን ያስረዳሉ፡፡ “መንግሥት መዋቅር ቢለውጥም ንጉሣዊ አገዛዙ ስላልተለወጠ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው ኃይል ከንጉሣዊ አገዛዙ ጋር ሊሄድ አልቻለም፡፡ የመንግሥት መዋቅሩ ለውጥ በጣም ፈጣን ሲሆን፣ ንጉሣዊ አገዛዙ የሚያደርገው ለውጥ እጅግ ዘገምተኛ ነበር፡፡ አዲሱ ኃይል በጣም ትዕግሥት ያጣ፣ መሄድ መወርወር አለብን የሚል ነበር፡፡ አባቶቹ የነበሩትን ጊዜ ጨርሶ አያመዛዝንም ነበር፤›› ብለዋል፡፡
አዲስ የፖለቲካ ባሕል
የተማሪዎች ንቅናቄ ብዙ በጎ ጎኖች ቢኖሩትም በርካታ አሉታዊ አሻራዎች እንዳሉት ያስታወሱት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ አብዮቱ በውስጡ ቀይ ሽብርን የፈጠሩ መሠረታዊ ምክንያቶች እንደነበሩትም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ምክንያት ቀኖናዊ የሆነ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተሳሰብ ማስረፅ ነው፡፡ ሁለተኛው የአመፅ ባሕል ፈጥሯል፡፡ ሦስተኛው የተፈጠረው ነገር ተፈጥሮአዊ ክፍፍል ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ሌላው የቀይ ሽብር ምንጭ የአመፅ ባሕል እንደሆነ ፕሮፌሰር ባህሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአመፅ ባሕል የተለያዩ ዘርፎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የሃይማኖት ዘርፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ወታደራዊ ዘርፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ጦርነት የተደረገው እርስ በርስ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ገለን መሸለል ባሕላችን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሦስተኛው የቀይ ሽብር ምንጭ የ1953 ዓ.ም. የእነ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሁለት አንድምታዎች አሉት፡፡ ሙከራው በመክሸፉ ከመንግሥት ይልቅ የተማሩት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ወታደሮቹ በተለይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ ማለት ሞት መሆኑን ተምረውበታል፡፡ ሌላው ሙከራው ከከሸፈ በኋላ ተሳትፎ አድርገዋል በተባሉት ሰዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ከቀይ ሽብር ጋር የተገናኘ ነበር፤›› በማለት አነፃፅረዋል፡፡
የቀይ ሽብር ውጤት ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን ወጣቶች በመፍጀት፣ አምባገነናዊ ሥርዓት በመፍጠርና ኅብረ ብሔራዊ ተቃውሞን በማክሰም እንደሚገለጽ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ቀይ ሽብር እንዳይደገም ከዝክር ባሻገር አዲስ ፖለቲካዊ ባሕል መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ጃፓንና ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፅልመት መጥተው ብሩህ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተዋል፡፡ ያ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በጀርመን በየጊዜው የሒትለር ሥራ በኤግዚቢሽን ይታያል፡፡ አዲሱ ትውልድ ያን እያየ ወላጆቹን ‹ይኼ ሁሉ ሲሆን ምን ታደርጉ ነበር?› ብሎ ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ይህን ለማምጣት አዲሱ ትውልድ ከሥር ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ቀይ ሽብርን እንዲያውቀው ማድረግና ዲሞክራሲን በተላበሰ መንገድ እንዲያድጉ መደረግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በውይይቱ ጥናት አቅራቢዎቹም ሆኑ ተሳታፊዎቹ አገሪቱ ወደፊት ልትሄድበት የሚገባው ጎዳና ሙሉ በሙሉ ከቀይ ሽብር የፀዳ እንዲሆን የተስማሙ ቢሆንም፣ በቀይ ሽብር ተፅዕኖ ስሜታዊነት ተስተውሎባቸዋል፡፡ ቢያንስ ግን በአንድ መድረክ መነጋገርና ሐሳብ መለዋወጥ (በአብዛኛው ራስን በመከላከል መንፈስ ቢሆንም) አንድ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የህወሓት ሁለቱ ቡድኖች (የመቐለና አዲስ አበባ) ዉዝግብ እንደቀጠለ ነው።

የህወሓት ሁለቱ ቡድኖች (የመቐለና አዲስ አበባ) ዉዝግብ እንደቀጠለ ነው።

የህወሓት ሁለቱ ቡድኖች (የመቐለና አዲስ አበባ) ዉዝግብ እንደቀጠለ ነው። በፖለቲካ ዘርፍ የአዲስ አበባው ቡድን ጥሩ እየተጫወተ ነው። አብዛኞቹ የመቐለ ቡድን አቀንቃኞች (ግን አዲስ አበባ አከባቢ የሚኖሩ) በሙስና ሰበብ እየታሰሩ (ሌሎችም እየደነገጡ) ከጨዋታ ውጭ እየሆኑ ሲሆን ለአዲስ አበባው ቡድን ደግሞ ዓቅም እያስገኙ ነው።

ግን የአዲስ አበባ ቡድን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ ይችላል የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱም የመቐለው ቡድን የትግራይ ክልል መንግስታዊ መዋቅር ለግል ፍላጎቱ በማዋል አብዛኞቹ የህወሓት አባላት በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየመከረ ነው። በትግራይ ክልል ቢሮ የሚሰራ የህወሓት አባል ለአዲስ አበባው ቡድን ለመደገፍ ይቸገራል። ምክንያቱም ለአዲስ አበባው ቡድን የደገፈ የትግራይ ባለስልጣን ከሓላፊነቱ ይባረራል። ስለዚህ አይሸናነፉም።
ይህ በንዲህ እንዳለ የህወሓት ሊቀመንብርና የትግራይ ክልል ፕረዚደንት የሆኑ አቶ አባይ ወልዱ ባለቤታቸው የሆኑት (ወይ የነበሩ) ወይዘሮ ትርፉ ኪዳነማርያም የህወሓት ፅሕፈትቤት ሓላፊና የፖለቲካ አማካሪ አድርገው ሽሟቸዋል። ይህ ስልጣን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀጥሎ በህወሓት ቁልፍ የሚባል ስልጣን ሲሆን የአቶ ቴድሮስ ሓጎስ የነበረ ነው።
እንዲህ ነው መተካካት። ባልና ሚስት ሁለቱም ቁልፍ ስልጣኖች ሲቆጣጠሩ። ‘ራእይን ማስቀጠል’ ካልቀረ እንዲህ ነው፤ የራስ ሚስት በቁልፍ ቦታ መሾም።
ህወሓት የፖለቲካ አማካሪዋን ይዛ ወደፊት። ጥሩ ነው፤ ትርፉ ኪዳነማርያም የህወሓት የፖለቲካ አማካሪ የምትሆንበት ዘመን። ህወሓቶች እንኳን ደስ አላቹ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በገንዘብ የአለማችን ሀብታም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የበቁ መሆናቸው ተዘገበ

“ዘ ሪቸስት ዳት ኦርግ” የተሰኘው ድረ-ገፅ ይፋ እንዳደረገው፤ የቀድሞው ጠ/ ሚ/ር መለስ ዜናዊ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት በመሆን ነው ከዓለማችን ፖለቲከኞች የሁለተኛ ደረጃን የያዙት።
“ዘ ሪቸስት” የተሰኘው ይህ ድረ-ገፅ፤ በአንደኛ ደረጃ ባለፀጋ ሲል ያሰፈራቸው የቀድሞውን የጣሊያን ጠ/ሚ/ር ሲልቪዮ በርሎስኮኒን ሲሆን አንደኛ ደረጃ ያስቀመጣቸውን የ5.9 ቢሊዮን ዶላር ያፈሩት ከፖለቲካው መድረክ ሳይሆን በሜዲያው መስክ ከተሰማሩበት ሥራ ነው።
የጣሊያኑ ሴሪአ የእግር ኳስ ክለብ የሆነው የኤ.ሲ. ሚላንና የቴሌሚላኖ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሎስኮኒ አሁንም የተንደላቀቀ ሕይወትን በመምራትና ዳንኪራ በመጨፈር የጣሊያንን ሜዲያዎች የፊት ገፅ የያዘ ፣ ርዕሰ-ዜና የሚሰራላቸው ታላቅ ሰው ናቸው ብሏቸዋል – ዘ ሪቸስት ዳት ኦርድ።
ከፍተኛ የገዘብ ምንጫቸው እንደሆነ የሚነገርለትና ላለፉት 25 ዓመታት በባለቤትነት የያዙት የአውሮፓው ታዋቂ የግር ኳስ ክለብ ኤሲ ሚላን ሲሆን፤ የ76 ዓመቱ በርሎስኮኒ በኢጣሊያ ቁጥር አንድ የሆነ የኢንተርቴይንመንት እንዲሁም የኢንሹራንስ፣ የባንክና የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያዎች ባለቤት ጭምር ናቸው።
በግላቸው ከነዚህ ዓይነት የንግድ ዘርፎች ጭራሽ የሌሉበት የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ከሊባኖሱ ጠ/ሚኒስትርና የንግድ ሰው ነጀብ ሚካቲ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት በመሆን የዓለማችን ሁለተኛ ባለፀጋ ፖለቲከኛ የተሰኙ ሲሆን የሀብት ምንጫቸው ፖለቲካ የተባለላቸው ሆነዋል።
በ3 ቢሊዮን ዶላር ጎን ለጎን ሆነው የተቀመጡት የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊንና የሊባኖሱን ጠ/ሚ/ር ነጂብ ሚካቲ የሚለያቸው የሀብት ምንጫቸው በአፍሪካ ያንሰራፉትና ያስፋፉት የቴሌኮም ኩባንያና ሌሎች የንግድ ሥራዎቻቸው ሲሆን የአቶ መለስ ዜናዊ ግን ፖለቲካ ብቻ መሆኑ ነው።
በዚህ የሀብታሞች ተርታ ሦስተኛ የተቀመጡት የሊባኖስ ጠ/ሚ/ር ሳድ አድን ራፊቅ አል ሐሪሪ ሲሆን የሀብት ልካቸውም 1.9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።
ታዋቂ የንግድ ሰው፣ ባለኩባንያና ፖለቲከኛው ራፊቅ አል ሐሪሪ የሃብት ምንጮቻቸውንም ቢዝነስ ነው ተብሏል በ ዘ ሪቸስት ዳት ኦርግ ዘገባ።
ከሴት ጠ/ሚ/ሮች የፓኪስታኗ ቤናዚር ቡቶ የ850 ሚሊዮን ዶላር ባለቤት ሆነው ከሴት ፖለቲከኞች በብቸኝነት ተጠቅሰዋል።
ያአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለቤታቸው በ6000 ብር ደመወዝ ሲተዳደሩ ቆይተው በድህነት ኖረው በድህነት የሞቱ መሆኑን በመግለፅ ሲከራከሩላቸው፣ እንዲያውም የዓለማችን ደሃና ጠንካራ መሪ ተብለው ሊፃፍላቸው ይገባል በማለት ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል።
Source: ኢሳት ዜና
መስከረም 19 ቀን 206 ዓ.ም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በጠራው ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የተደረገ ንግግር
-----------------------------------------------------

 



የተከበራችሁ የሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚዎች፤
የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤
የተከበራችሁ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች፤
ክቡራንና ክቡራት!

አስቀድሜ የማክበር ሰላምታየን እያቀረብኩ መብታችንን አደባባይ ወጥተን ለምንጠይቅበት፣ ያልተሸራረፈ ነፃነታችንን ለማረጋገጥ ጉዞ ወደቀጠልንበት ታሪካዊ ቀን ሁላችንንም እንኳን አደረሰን፡፡

በመቀጠልም ለዚህ ዝግጅት መሳካት የተባበሩንን፣ የረዱንን፣ ያገዙንንና በቅስቀሳ ወቅት መስዋዕት ከፍለው ለዚህ ላደረሱን የአንድነትና የ33ቱ አባላት፣ አመራሮችና ደጋፊዎቻችን ከፍ ያለ ምስጋናየን ከአክብሮት ጋር ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በስትራቴጅው መሰረት በመጀመር፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በማንቀሳቀስ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማከናወኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነገር ግን ሕጋዊ መብቱን ሳያስነካ፤ መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በመክፈልና በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት ከአባላቱና አመራሩ ጋር በመሆን በማከናወን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መመኪያ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ዛሬ የተሰለፍንበት ዋና ምክንያትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሰለፈለትን፣ የሞተለትን፣ በአጠቃላም አንድ ትውልድ ትልቅ ዋጋ የከፈለለትን ግን ደግሞ እስካሁን መረጋገጥ ያልቻሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ የሰፈነባት የሁላችን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲደረግ የቆየውን ትግል በማያዳግም መልኩ ከህዝቡ ጋር በመሆን እውን ለማድረግ ነው፡፡

የምንታገለው ለመብታችን መከበር፣ ለነፃነታችን መረጋገጥ፣ ለሀገር ሉዓላዊነታችን፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ የታሰሩ የፖለቲካና ህሊና እስረኞች እንዲፈቱና ማንም ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ፣ በእምነቱና ሃሳቡን በነፃነት ስለገለፀ የማይታሰርባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲሁም የፀረ-ሽብር ህጉ መሰረታዊ ዜጎችን መብቶችና ሕገ-መንግስቱን በግልፅ የሚንድ በመሆኑ የሚሊዮኖችን የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሰረዝ ለማድረግ ነው፡፡

ዛሬ የተሰለፍነው ኢህአዴግና የኢህአዴግ መንግስት እንደሚከሰን ሁከት ለመፍጠር አይደለም፣ ሽብር ለመፍጠር አይለም፣ አሸባሪዎች ስለሆንን አይደለም፣ የአሸባሪዎች መደበቂያ ስለሆንንም አይደለም፣ የሻዕቢያ መልዕክት አድራሾች ስለሆንን አይደለም፣ በአቋራጭ የመንግስት ስልጣን ለመያዝም አይደለም፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በገዥው ፓርቲ የተነጠቅናቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስመለስ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በአመለካከታችን የማንታሰርባት ኢትዮጵያ ስለምታስፈልገን ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የተሰለፍነው በጉልበትና አፈና መግዛት እንዲበቃና እንደሌሎች ሀገሮች ሀገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንድትሆን ነው፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
ፓርቲያችን አንድነት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚገባትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ በሰላማዊ የትግል መስመር ለማረጋገጥ ትግል ከጀመረ አምስት ዓመቱን ይዟል፡፡ በነዚህ ዓመታትም ፓርቲያችን ወደ ፍፁም አምባገንነት እየሄደ ያለውን ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ አካሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጠቃ እንዲቆም አጥብቆ ታግሏል፣ እየታገለም ይገኛል፡፡

በትግሉ ሂደትም ስርዓቱ በግልፅና በስውር ፓርቲያችን ላይ ጥቃት ፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል፡፡ አመራሮቻችንና አባሎቻችንም ስለ ቁርጠኛ ዓላማቸው ያለምንም ማፈግፈግ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ስለ ዴሞክራሲና ነፃነት ሲሉ ጨለማ ክፍል የተጣሉትን ወጣት የፖለቲካ አመራሮች፣ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ እስር ቤት የተጣሉ ጋዜጠኞችና የዕምነት ጣልቃ ገብነትን የተቃወሙ የሙስሊም ወገኖች መፍትሄ አፈላላጊ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቀለን፡፡ ዜጎችን ለማሰር እያገለገለ ያለው የጸረ-ሽብር አዋጅም በአስኳይ እንዲሰረዝና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እየሰሩ ያሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ውይይት እንዲጀመርና በሀገራችን ጉዳይ ላይ መፍትሄ እየሰጠን እንድንሄድ፤ ለዚህም ገዥው ፓርቲ ፈቃደኛም፤ ቁርጠኛም እንዲሆን ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ በኢህአዴግ ብቻ አይፈታም፡፡ በሌላ አንድ ፓርቲ ብቻም ይፈታል ብለንም አናምንም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመተባበር፣ በመቀናጀትና ውህደት በመፍጠር ትልቅ የፖለቲካ አቅም መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

የተከበራችሁ ሰላማዊ ሰልፈኞች!

አሁንም ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ለውጥና ማሻሻያ ለማድረግ ፍላጎትም አቅምም የለውም፡፡ በ3 ወር ህዝባዊ ንቅናቄችን ያረጋገጥነው ይሄንኑ ነው፡፡ ምክንቱም አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዥ ሀይል በሰላማዊ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ አሁንም ለጥያቄ አቅራቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ቢሆን ህዝባችን ጋር ለመድረስና ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለማሰማት ችለናል፡፡ ይሄው በማሰማት ላይም እንገኛለን፡፡ ሰላማዊ የተቃውሞ ትግላችንን አጠናክረን በመቀጠል አምባገነኖችን በሚያንቀጠቅጥ የተቃውሞ ትግል እንደምናሸንፍ አልጠራጠርም፡፡

በጎንደርና ደሴ ከተማ በ7/11/2005 የጀመርነው የተቀውሞ ሰልፎች በባህርዳር፣ በአርባምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማ፣ በፍቼ በተሳካ ሁኔታ የተካሄዱ ሲሆን በመቀሌና ባሌ ሮቤ በከፍተኛ ጫናና ህገወትነት ሳካሄዱ ቀርተዋል፡፡ በወላታ ሶዶና አዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡ ከላይ በጠቀስናቸው ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ ደብድበዋል፣ አዋክበዋል፡፡ ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን አግተዋል፣ የተለጠፉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማካሄዳቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅና በጉልበት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ችለናል፡፡

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን!

ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ተቋምና የፍትህ ስርዓት ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የፖሊስና የደህንነት ተቋምም ያስፈልገናል፡፡ ነፃና ገለልተና የዴሞክራሲ ተቋማትም መፈጠር አለባቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ተቋማት የሚፈጠሩት ግን በልመና አይደለም፡፡ እነዚህን ተቋማት ነጻ ሆነመው እንዲፈጠሩ የምታደርጉት እናንተ ናችሁ፡፡ ነፃነት ከፍርሀት አይገኝምና፣ በሀገር ጉዳይ አይፈራምና ነፃነታችንንና መብታችንን የሚነጥቁንን እምቢ ማለት አለብን፡፡ አትችሉም ማለት አለብን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ገዥዎችን የምንፈራብ ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ ገዥ ህዝቡን ይፈራል እንጅ ሕዝብ ገዥዎችን አይፈራም፡፡

ከላይ የተናገርኩትን የሚያጠናክር መረጃ ላቅርብ፡፡ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይያዛሉ፣ አስገድው በአካል ፈሳሽና ናሙና በመውሰድ ምርመራዎች ይካሄዳሉ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ በውሸት ማስመስከርና አስገድዶ መረጃ ማውጣጣት፣ ቶርቸር፣ ዜጎች በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ ማስገደድና ሌሎች የማሰቃያ ዘዴዎች አገዛዙ ፍርሃት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ስርዓቱ ዜጎች ካላግባብ ከየመኖሪያ ቀያቸው በገጠርም ሆነ በከተማ በግፍ እንዲፈናቀሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄው ሀገራዊ ይዘት ያለው ማፈናቀል ሦስት አይነት መልክ ያለው ሲሆን በዘር ላይ ተመሰረተ ማፈናቀል፣ በልማት ስም ማፈናቀልና ለመሬት ወረራ ማፈናቀል ናቸው፡፡ ዘርን መሰረት ያደረገው ማፈናቀል በቅርቡ ብቻ በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎችና ሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተው ነው፡፡ በልማት ስም የሚከናወነው ማፈናቀል በአብዛኛው በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው መሰረቱ የገዥው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡ መሬት በባለቤቱ ፈቃድ የሚሸጥና የሚለወጥ ባለመሆኑ ያለበቂ ካሳና ማስጠንቀቂያ ለማህበራዊ ትስስር ቁብ ሳይኖረው ልማት የሚል ስም ብቻ በማንሳት ዜጎች የሚፈናቀሉበት ነው፡፡ ሌላው የማፈናቀል አይነት ደግሞ ከመሬት ወረራ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና በእርሻ መሬት ሰበብ ዜጎች እየተፈናቀሉ ለውጭና ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በጥቂት ሳንቲም የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄም በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች በስፋት የታየና እየታየ ያለ ነው፡፡ ሀገራቀፉን ማፈናቀል አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በአስቸኳይ እንዲቆምም እንጠቃለን፡፡

ከመፈናቀሉ በተጨማሪም ቅጥ ያጣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ ያስነካው የዋጋ ግሽበት ዋና መንስኤው ስርዓቱ የሚከተለው የተሳሳተ አጠቃላይ ፖሊሲ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ የወለደው ነገር ቢኖር ሀገራችን በታሪኳ አይታ የማታውቀው ስደት ነው፡፡ ዜጎች ከፊት ለፊት ሞት እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ተጋፍጠው ለስደት የመነሳታቸው መንስኤ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር የነፃነት እጦት ሲታከልበት የችግሩን መልክ ውስብስብ አድርጎታል፡፡

የንግዱን ማህበረሰብም ስንመለከት ከመቼውም በባሰ ሁኔታ ነጋዴ መሆን ወንጀለኛ መሆን የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ በተጨማሪም አንድ ፓርቲ ነጋዴና አንድ ፓርቲ ህግ አውጭ በሆነበት ሁኔታ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ስለዚህ የግሉ ሴክተር የልማት ሚና አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ካላግባብና በግምት የሚጣል ታክስ መክፈል ሃገራዊ ግዴታ የመሆኑን ለዛ አሳጥተውታል፡፡ አንዳንዱ በብልጣብልጥነት ስርዓቱን እንደመታወቂያና ከለላ በመጠቀም፣ ከባለስልጣናት ጋር በመሻረክ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሀብት ማማ ላይ ሲወጣ እንመለከታለን፡፡ ይሄም በንፁህ ንግድ ላይ ያልተመሰረቱ ለበርካታ ዜጎች አደጋ ነው፡፡ ከዚያም ልቆ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሃዊ የንግድ አሰራር እንዲኖር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ማስገንዘብ የምወደው በሀገራችን የስልጣን ሽግግር ታሪክ እንዱ እንዱን በአፈሙዝ እየገደለ፣ መንድም ወንደሙን ጠላት እያደረገ ነው፡፡ ይህም የርስ በርስ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ትውልድ ብቻ ሁለት አብዮቶች ተካሂደዋል፡፡ በአገራችንንና በትውልዱ ላይም በገንዘብ የማይተመን ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ዛሬም በተለይም ወጣቱ ትውልድና ዋጋ የከፈሉ አባቶች ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ምኞታችን ከፍተኛ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ እየዘጋው ያለው ዴሞክራሲያዊ መንገድና ዜጎች እየደረሰባቸው ካለው ስቃይ አንፃር ወደ ሕዝባዊ አመፅ ተቀይሮ ወደ ሶስተኛው አብዮት ቢገፋ ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክትም ምንም እንኳ የወረሳችሁድ ዕዳ ብዙ ቢሆንም በቁርጠኝነት ታግላችሁ ሀገራችንን እንደሰለጠኑት ሀገሮች እንደምታደርጉ ተስፋ አለኝ፡፡ ከ50 ዓመት በላይ ዋጋ የተከፈለበት ዴሞክራሲ እውን እንድታደርጉ አደራ እያልኩ እንደምታሳኩትም ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ግንቦት7 በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ መስመሩን እየዘረጋ መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናገሩ

ግንቦት7 በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ መስመሩን እየዘረጋ መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናገሩ

 ግንቦት7 በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ መስመሩን እየዘረጋ መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናገሩ
መስከረም ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ አንዳርጋቸው ይህንን የተናገሩት በኖርዌይ ከተካሄደው ደማቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሁዋላ ነው።
የግንቦት7 ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ በአንድ በኩል በግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል አባላት ላይ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር በሌላ በኩል ደግሞ የተጣለብን ህዝባዊ አደራ ከፍተኛ መሆኑን የሚያስታውሰን ነው ብለዋል።
በቅርቡ ከኢትዮጵያ አየር ሀይል ከድተው የሄዱት ሰዎች በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው ፣ በመከላከያ ሰራዊት በእግረና፣ በአየር ሃይልና በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሊደርሱበት በማይችሉበት መንገድ መስመር እየዘረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በውጭ አገራት ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ለማድረግ እቅድ አላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ አንዳርጋቸው፣ ህዝባዊ ሀይሉ ከተግባር ጋር በተዛመደ መልኩ የገቢ መሰባሰብ ዝግጅት መርሀ ግብሩን ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ በህዝባዊ ሀይሉ ወይም በግለሰቦች ስም ምንም አይነት የገቢ መሰባሰቢያ ዝግጅት መደረግ እንደሌለበት ገልጸዋል
በሌላ ዜና ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው በስቶክሆልም እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ውይይት አድርገዋል። አቶ አንዳርጋቸው የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልን ዓላማዎች፡ተልዕኮዎች እና ራዕይ በማስተዋወቅ ህዝባዊ ሃይሉ ከምስረታ ጀምሮ አሁን ያለበትን ደረጃ በምስልና በጽሁፍ የተደገፈ ገለጻ ለተሰብሳቢው አቅርበዋል።
እሳቸው እና ሌሎች የአመራር አካላት እንዲሁም አባላት የተገኙበት የውትድርና ስልጠና አንዱ የበታች አንዱ የበላይ እንዳልሆነ በማስገንዘብ ይህ ህዝባዊ ሃይል ቤተሰባቸውን፡ስራቸውን፡ ገንዘባቸውን፡ እና የተደላደለ ኑሯቸውን በመተው ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን የተዋቀረ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግንቦት ሰባት ዓላማ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ብቻ ሳይሆን ባለፉት 22 ዓመታት ኢትዮጵያውያን የተገፈፉትን ክብራቸውን ማስመለስ ጭምር መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው አስምረውበታል ሲል ቴዎድሮስ አረጋ ከስዊድን ዘግቧል።
ESAT